አስረኛው የመላ ጋምቤላ ዓመታዊ የወረዳዎች የስፖርት ውድድር በመኮይ ወረዳ ኚንኛንግ ከተማ ዛሬ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አስረኛው የመላ ጋምቤላ ዓመታዊ የወረዳዎች የስፖርት ውድድር በመኮይ ወረዳ ኚንኛንግ ከተማ ዛሬ ተጀመረ
ጋምቤላ (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 አስረኛው የመላ ጋምቤላ ዓመታዊ የወረዳዎች የስፖርት ውድድር በመኮይ ወረዳ ኚንኛንግ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።
በስፖርት ውድድሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ውድድሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት ስፖርት ለአንድ ሀገር ከሚኖረው ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በተጨማሪ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ማህበራዊ ረገድም የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በመሆኑም ውድድሩ ጨዋነትን በተላበሰና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ፍፃሜውን እንዲያገኝ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ውድድሩ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ለመምረጥና ለማብቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ርዕሰ-መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በባህልና ሰፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በስነ-ስርዓቱ ለይ እንዳሉት ዓመታዊ የስፖርት ውድድሩ ምርጥ ስፖርተኞች የሚመለመሉበት መድረክ ነው ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ወጣቶች ተክለ ቁመና ለየትኛውም የስፖርት ዓይነት ምቹ የሆነና ሀገርን ወክለው የሚወዳደሩ ስፖርተኞች መፍለቂያ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ክልሉ ለዘርፉ መጠናከር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ቱት ኮር ክልሉን የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት ኮምሽኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዕለቱ የተጀመረው 10ኛው የመላ ጋምቤላ ዓመታዊ የወረዳዎች ስፖርት ውድድር የጥረቱ አካል መሆኑንም ገልጸዋል።
በመኮይ ወረዳ አዘጋጅነት ከዛሬ የካቲት 4 ቀን 2015 ጀምሮ ለ15 ቀናት በሚቆየው ውድድር የጋምቤላ ከተማ አስተዳድርን ጨምሮ 12 ወረዳዎች በእግር ኳስ፣ በመረብና በቅርጫት ኳስ፣ በአትሌቲክስና ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች በርካታ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉበት ከወጣው መረሃ-ግብር ለማወቅ ተችሏል።