በወላይታ ሶዶ ከተማ ኢንቨስትመንት በማስፋት የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው - የሶዶ ከተማ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ ኢንቨስትመንት በማስፋት የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው - የሶዶ ከተማ አስተዳደር
ሶዶ (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 በወላይታ ሶዶ ከተማ የኢንቨስትመንት መስኮችን በማስፋት ከተማዋን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ገለፀ።
የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተመስገን አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በኢንቨስትመንት መስክ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ለመሳብ የማስተዋወቅ ሥራ እየተካሔደ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን በዘርፉ ለመሰማራት የሚመጡ ባለሃብቶች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙና ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 18 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የቀረቡ ሲሆን ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የተጀመሩ ነባር ፕሮጀክቶችም በተሟላ መልኩ የኢንቨስትመንት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ የድጋፍና ክትትል ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።
በከተማዋ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት መሬት ወስደው እስካሁን ወደ ሥራ ያልገቡ ባለኃብቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጥናት መካሄዱንም ተናግረዋል።
በጥናቱ ውጤት መሰረትም ከባለሃብቶቹ ጋር በመወያየት ወደ ሥራ መግባት ለሚችሉት ድጋፍ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ወደ ሥራ መግባት በማይችሉት ላይ ደግሞ የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰድም ነው የተናገሩት።
ባለሃብቶች በከተማዋ በንግድ፣ በቤት ልማት /ሪል-ስቴት/ ግንባታ፣ በአምራች ኢንደስትሪ፣ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ መሰማራት የሚችሉበት ሰፊ እድል መኖሩን አስታውቀዋል።
በከተማዋ መዋእለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሃብቶች በቂ የሰው ኃይል፣ የኤሌክትሪክ፣ የመንገድ፣ የውኃና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች እንደሚመቻችላቸው ነው የተናገሩት።
የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ አስተባባሪ አቶ ፍሬህይወት ወልደ-መስቀል ፣ ባለሃብቶች በከተማዋ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እየተሰማሩ ነው።
ከ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት አንስቶ ከ150 በላይ የሚሆኑ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን ለሰራ አጥ ወጣቶችም በርካታ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እየፈጠሩ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ወደ ስራ እንዲገቡ የተሻለ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ነው ያረጋገጡት።
ባለፉት አራት አመታት የሶዶ ከተማን የተሻለ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በዘርፉ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም የሶዶ ከተማን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ የቱሪዝምና ኮንፍረንስ ማዕከል እንድትሆን ሰፊ እድል ማበርከቱንም አስታውቀዋል።
ከተማዋን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች በማከናወን ለባለሀብቶች ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።