ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታልን ወደ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 የኢትዮጵያ ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታልን ወደ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳደግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የፖሊስ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ታድመዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የጤና አገልግሎት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዶክተር ደረጀ ተካልኝ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ በየደረጃው ለሕሙማን የሚሰጠውን አገልግሎት እያሳደገ ነው።

በአነስተኛ ክሊኒክ ደረጃ ሥራውን የጀመረው ሆስፒታሉ፤ በአሁኑ ወቅት በሪፈራል ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ነው የገለጹት።

በቀጣይም አገልግሎቱን ወደ ኮምፕሬሄንሲቭ /የተቀናጀ/ ደረጃ ለማሳደግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው የተናገሩት።

ሆስፒታሉ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትም በርካታ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በተለያየ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የሰራዊቱ አባላት የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ከተመሰረተበት 1954 ዓ.ም ጀምሮ ለሠራዊቱ አባላትና ቤተሰቦች ህክምና እየሰጠ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው።

ሪፈራል ሆስፒታሉ በመላው ሀገሪቱ ከ50 በላይ ጤና ተቋማትን ከፍቶም ለአባላቱና ለቤተሰቦቻቸው የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም