ቀጥታ፡

ለሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ የሚመጡ እንግዶችን በጥሩ መስተንግዶ በማስተናገድ የአገር በጎ ገጽታን ለማስተዋወቅ ተዘጋጅተናል--የሆቴል ኃላፊዎች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚመጡ እንግዶችን በጥሩ መስተንግዶ በማስተናገድ የአገርን በጎ ገጽታ ለማስተዋወቅ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የሆቴል ኃላፊዎች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ የሚጀምረውን 36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ትገኛለች።

የጉባዔው ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ አገልግሎት ከሚያገኙባቸው ተቋማት መካከል የሆቴል ዘርፉ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

ይህን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሆቴል ባለንብረቶች የሕብረቱን ጉባዔ ለመካፈል ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የተለያዩ አገራት እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል የሽያጭ ዳይሬክተር ሰይፈዲን ባዲ፤ የተለያዩ አገራት መሪዎች የሚያርፉባቸውን ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

እንግዶችን በጥሩ ኢትዮጵያዊ አቀባበል በማስተናገድ የአገር ገጽታን መሸጥ በሚያስችል መልኩ መዘጋጀታቸውን ጨምረዋል ገልጸዋል።

የኢንተር ሌግዥሪ ሆቴል የሽያጭና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ወገኔ ታደሰ በበኩላቸው፤ 36ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔን ከተጠቃሚነት ባለፈ የአገር ገጽታን ለመገንባት እንደ ትልቅ አጋጣሚ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። 

የተለያዩ አገራት ልዑካን ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ሲጀምሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጀምሮ በመቀበል የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። 

በቆይታቸውም ከአለባበስ ጀምሮ ኢትዮጵያ ያላትን እሴት በማስተዋወቅ ከጉባዔው ባለፈ ለጉብኝት ምርጫቸው እንዲያደርጓት ለመሥራት ተዘጋጅተናል ሲሉም አክለዋል። 

 የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ማርኬት ማኅበር ፕሬዝዳንት ጌታሁን አለሙ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሆቴል ኢንዱስትሪው የደረሰችበትን ደረጃ በመጠቀም ለእንግዶች አገልግሎት ለመስጠት ከሆቴል ኃላፊዎች ጋር ቅድመ-ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። 

ሆቴሎች በሚሰጡት አገልግሎት ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ በሚያስችል መልኩ እንዲሆን ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት። 

ሆቴሎች የሚያስተናግዱት የአንድን አገር መሪ ከመሆኑ አንጻር አገልግሎታቸውን የአገርን ገጽታ የሚያስተዋውቅ ልዩ መስተንግዶ ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።  

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ 148 ባለ ኮከብ ሆቴሎች የሚገኙ ሲሆን፤ የአልጋ ብዛታቸው ወደ 12 ሺህ ይጠጋል። 

36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 41ኛው የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም