የአፍሪካ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስርን በማጠናከር የጋራ ምጣኔ ሃብታዊ እድገትን ማሳለጥ ይኖርባቸዋል - የአፍሪካ ኤሌክትሪክ ኃይል ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስርን በማጠናከር የጋራ ምጣኔ ሃብታዊ እድገትን ማሳለጥ ይኖርባቸዋል - የአፍሪካ ኤሌክትሪክ ኃይል ማህበራት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 የአፍሪካ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስርን በማጠናከር የጋራ ምጣኔ ሃብታዊ እድገትን ማሳለጥ እንደሚገባቸው የአፍሪካ ኤሌክትሪክ ኃይል ማህበራት ገለጹ።
የኬንያ ታዳሽ ኃይል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንድሪው አማዲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የኃይል አቅርቦት ሳይኖር እድገትን ያስመዘገበ አገር እንደሌለ ገልጸው፤ ታዳጊ አገራትም የኃይል አቅርቦትን ለምርት እድገት በመጠቀም እሴት በመጨመር ለገበያ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
ትርጉም ባለው መልኩ የመልማት ግብን ለማሳካት የኃይል አማራጭን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ለዚህም አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስራቸውን በማስፋት ምጣኔ ኃብታዊ እድገታቸውን በማሳለጥ የዜጎችን በጋራ የማደግ ፍላጎት እውን ማድረግ እንደሚኖርባቸውም መክረዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ከተቻለም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የኢንቨስትመንት መሰረተ- ልማት ወጪዎችን መቀነስ ያስችላልም ብለዋል።
በአፍሪካ የሚካሄዱ የንግድ ልውውጦችን በማሳለጥ ለአህጉሪቷ ለኢኮኖሚ ውህደት እንቅፋት የሆኑ መሰናክሎችንም ማስወገድ እንደሚገባ አንስተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናም በመተባበር ለጋራ እድገት መሥራት የሚያስችላቸውን የግብይት ሥርዓት በመፍጠር ያለውን ከፍተኛ የገበያ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአፍሪካ የኃይል አገልግሎት ማኅበር (ኤ.ፒ.ዩ.ኤ) ዋና ዳይሬክተር አቤል ዲዳየር ቴላ፤ አገራት በኃይል አቅርቦት ዘርፍ መዋዕለ-ንዋያቸውን በማፍሰስ የመልማት ፍላጎትን ማሳለጥ የሚችል የኃይል አቅርቦት መገንባት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ልማት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግሥታትም በኃይል ልማት ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ጥሬ እቃ ላይ እሴት በመጨመር አምርቶ መሸጥና መለወጥ መቻልም ከድህነት ለመውጣት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት ላይ ውጤታማ ሥራ በማከናወን የውጭ ምንዛሬዋን በማሳደግ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ለማስተሳሰር እየሰራችው ያለው ሥራም የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማሳለጥ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናውን የኃይል አቅርቦት በማሳደግ ምጣኔ ኃብታዊ ትስስርን ለማሳለጥ ለሱዳን፣ ጂቡቲ እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች።