አዲሱ የዓባይ ድልድይ ግንባታ 91 በመቶ ተጠናቋል-የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የዓባይ ድልድይ ግንባታ 91 በመቶ ተጠናቋል-የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 በባህር ዳር ከተማ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ እየተገነባ ያለው አዲሱ የዓባይ ድልድይ ግንባታ ከ91 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክቱ ኢንጂነር ለሚ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አዲሱ የዓባይ ድልድይ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ በአገራችን ከሚገኙ ድልድዮች የተለየ ነው።
ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በአንድ ጊዜም ስድስት መኪኖችን ለማስተላለፍ እንዲያስችል ተደርጎ እየተገነባ ነው ብለዋል።
ድልድዩ በግራና ቀኝ 3 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው የሳይክል መስመር እንዲሁም 5 ሜትር ስፋት ያለው የእግረኛ መንገድ አካቶ እየተሰራ ሲሆን፣ ለከተማዋ እድገትም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የድልድዩ የግንባታ ሥራ አየተከናወነ ያለው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም መሆኑን ያነሱት ኢንጂነር ለሚ በአሁኑ ወቅት የድልድዩ ግንባታ ሥራ ከ91 በመቶ ባላይ የደረሰ ሲሆን፣ በመጪው ሰኔ 2015 ዓ.ም ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ብለዋል።
የቻይናው ሲሲሲ ኩባንያ ቴክኒካል ማናጀር ሚስተር ዊ ኬትክንግ ድልድዩ በርካታ ኬብሎችና ትላልቅ የምሰሶ መወጠሪያ ያለው በመሆኑ በረጅም ጊዜ ከማገልገል ባለፈ ከፍተኛ ክብደት የመሸከም አቅም እንዳለው አስረድተው ለከተማዋም ተጨማሪ ውበት እንደሚሆን አመልክተዋል።
በፕሮጀክቱ በቅየሳ ሙያ የሚያገለግለው እንዳልካቸው ማሞ በበኩሉ ፕሮጀክቱ ግዙፍ መሆኑ አዳዲስ እውቀትና ልምድ ለማግኘት እንዳስቻለው ገልጿል።
ፕሮጀክቱን ተከትሎ ግዙፍ ሕንጻዎች፣ መዝናኛዎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተገነቡ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ለባህር ዳር ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክቷል።
አዲሱን የዓባይ ድልድይ ከባህር ዳር ከተማ ዋና ዋና መስመሮች የሚያገናኙ መንገዶች ግንባታም በመከናወን ላይ መሆኑን ለመመልከት ተችሏል።
የድልድዩን ግንባታ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ በ2011ዓ.ም ቢጀመርም በኮቪድና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ከ300 ቀናት በላይ መዘግየቱ ለማወቅ ተችሏል።