ቀጥታ፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና 45ኛ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ላይ ይካሄዳል።

ፈረሰኞቹና ቡናማዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ በፕሪሚየር ሊጉ 45ኛው ግንኙነታቸው ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና 7 ጊዜ አሸንፏል፤ 16 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በነዚህ 44 የሊግ ጨዋታዎች 88 ግቦች ሲቆጠሩ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ 60 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 28 ግቦችን አስቆጥረዋል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ጊዜ አሸንፏል። አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 28 ጎል ሲያገባ የተቆጠረበት 7 ብቻ ነው። በ21 የግብ ክፍያ በ25 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

This image has an empty alt attribute; its file name is 330815720_847089896393998_2499432313520645025_n.jpg

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና 12 ጨዋታዎችን አድርጎ አምስቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 16 ግቦች አስቆጥሮ 14 ተቆጥረውበታል።

በሁለት የግብ ክፍያ በ17 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ ቡና በውጤት ማጣት ምክንያት በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ማሰናበቱ የሚታወስ ነው።

ዮሴፍ ተስፋዬ ቡናማዎቹን በጊዜያዊነት በማሰልጠን ላይ ይገኛል።

በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገውን “የሸገር ደርቢ” ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ያላቸው የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ለጨዋታው ድምቀት እንደሚሰጡት ይጠበቃል።

የሁለቱን ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም