ቀጥታ፡

የግብርና ሚኒስትሩ በመስኖ ልማት፣ በገበያ ትስስርና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ላይ ከዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 3/2015 የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በመስኖ ልማት፣ በገበያ ትስስርና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ላይ ከዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) የኢትዮጵያ ተወካይና ዳይሬክተር ማዊራ ቺቲማ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።


ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ድጋፍ በተከናወኑ ስራዎች ፣በተገኙ ውጤቶችና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ስራዎች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።


በቀጣይ በመስኖ ልማት፣ በገበያ ትስስርና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።


በውይይቱ የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ውሃን በሰፊው ለልማት ለማዋል በሚደረገው ሂደት በመስኖ ልማት ስራዎች በልዩ ትኩረት ይሰራል ተብሏል።


ዶክተር ግርማ የውሃ አማራጮችን በሰፊው ለልማት ለማዋል ግብርና ሚኒስቴር፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ሚኒስቴር በጋራ መስራት አለባቸው ብለዋል።


ከሚታረሰው 14 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 7 ሚሊዮን ሄክታር ወይም 50 በመቶ በአሲድ የተጠቃ መሆኑ አሳሳቢ ነው ያሉት ዶክተር ግርማ በቀጣይ በአፈር ለምነትና ጤንነት ላይ እንሰራለን ብለዋል።


በቀጣይ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ከ9 መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ በማድረግ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ልማቶችን እየሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ በአነስተኛ መስኖ ልማት የአርብቶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የብድርና ቁጠባ አገልግሎትን ለማመቻቸት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም