የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያለውን ድርሻ ለማስፋት ይሰራል - የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያለውን ድርሻ ለማስፋት ይሰራል - የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር
አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 3/2015 የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ያለውን ድርሻ ለማስፋትና አገሪቱ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ገለጸ።
የማኅበሩ የቦርድ አመራሮችና አባላት ማኅበሩ የተመሰረተበት የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኤዮቤልዩ በዓል አከባበርን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
የማኅበሩ ፕሬዘዳንት አቶ ደሳለኝ ገና በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ማኅበሩ ጠቃሚ የፖሊሲ ኃሳቦችን በማመንጨት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ገበያ ተጠቃሚ እንድትሆን እየሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በዓለም በምርት አቅርቦት በ5ኛ ደረጃ እንዲሁም በገበያ ድርሻ ደግሞ 9ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህንን ደረጃዋን ለማሻሻል ማኅበሩ ይሰራል ብለዋል።
በተለይም ከጥራት በተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ተቀባይነት ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
በቡና ግብይት ላይ የወጡ የሕግ ማሻሻያዎች አምራቹ በቀጥታ ከገበያው ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸው ይህም ለዘርፉ እድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቁመዋል።
ማኅበሩ በቀጣይ ዓመታት የቡና ምርምር፣ የላብራቶሪ ማዕከልና ሌሎች ክፍሎችን ያቀፈ ሁለን አቀፍ ሙዚየም ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበሩ በኮቪድና በተለያዩ ችግሮች የማኅበሩ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኤዮቤልዩ በዓሉን ሳይከበር መቆየቱን ገልጸው የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ በአዲስ አበባ እንደሚከበር ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር መጋቢት 20 ቀን 1961 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር” በሚል ስያሜ በ12 አባላት በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመሰረተ ማኅበር ነው።