ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ተዳክሞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ እየተነቃቃ መጥቷል-የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ

ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 3/2015 በአማራ ክልል በኮቪድ-19 እና በጦርነት ምክንያት ተዳክሞ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ በተገኘው ሰላም ዳግም እየተነቃቃ መምጣቱን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። 

ከ11 ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እና ከ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች በክልሉ በተከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ላይ መገኘታቸውም ተመልክቷል።  

በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አደም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ክልሉ ቱሪስቱን የሚስቡ በርካታ የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት ነው።

በክልሉ የሚካሄዱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት፣ የላሊይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲል ግንብ፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጭስ ዓባይ ፏፏቴና ሌሎች የቱሪዝም ሃብቶች በዋናነት እንደሚጠቀሱም ተናግረዋል። 

በተያዘው ዓመት ዘርፉን ለማነቃቃት በተሠራው ሥራና በተፈጠረው ሰላም እስከ ጥምቀት በዓል ድረስ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። 

ገቢው የተገኘው ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ ከ11 ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እና ከ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች መሆኑንም ተናግረዋል። 

"በተለይም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ ነው" ያሉት አቶ መልካሙ፣ ይህም የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ክልሉ የመጡት የአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል የልጃ ገረዶች ፌስቲቫልን እንዲሁም በላሊይበላ የሚከበረውን ገና፣ በጎንደር ጥምቀትን፣ የግሸን ማርያም በዓላትን ለመታደምና አካባቢዎቹን ለመጎብኘት ነው። 

ገቢው በሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ በስጦታ እቃ መሸጫ ሱቆች፣ የማጓጓዣና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ የተገኘ መሆኑን አስረድተዋል። 

በክልሉ የጎብኚዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ81 በመቶ በላይ እድገት ማሳየቱን ጠቁመው፤ "ይህም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት አስችሏል" ብለዋል። 

በክልሉ በሚከበሩ ዋና ዋና ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ህብረተሰቡና ኩባንያዎች ጭምር ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል። 

በተጨማሪም የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥና የአሀገርን ገጽታ በመገንባት በኩል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ነው ዳይሬክተሩ ያመለከቱት። 

ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሪከርድ በሆነ መልኩ ለጥምቀትና ለገና በዓላት ወደ ጎንደርና ላሊበላ 97 በረራዎችን በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አቶ መልካሙ ተናግረዋል። 

በክልሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ የፀጥታ ሃይሉ፣ ወጣቶችና መላው ህብረተሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። 

ዘንድሮ የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋት የቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ እንዲነቃቃ የሚያስችሉ ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም