ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች እገዛ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች እገዛ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 3/2015 በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች እገዛ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጥሪ አቀረቡ።
ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን በትላንትናው ዕለት 442 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ሚንስቴር ድጋፍ አድርጓል።
የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች የተፈተነችበት ወቅት እንደነበር ገልፀው በጤናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ የተለያዩ አካላት በሚያደርጉት ቀና ትብብር በጤናው ዘርፍ ላይ ያጋጠሙ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድንም ለሚንስቴሩ ላደረገው የህክምና ቁሳቁስ ላበረከቱ አካላትና ሌሎች ድጋፉ እውን እንዲሆን ለሰሩ ምስጋና አቅርበዋል።
ዶክተር ሊያ በቀጣይም ሚንስቴሩ በጦርነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማቶች ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባትና የጤና ዘርፉን ለማዘመን የጀመረው ስራ እንዲሳካ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ይሰራል ብለዋል።
አጋር ድርጅቶችም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን ዳይሬክተር አለማየሁ አበበ በበኩላቸው ለሕክምና አገልግሎት የሚያገለግሉ ከ8 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ልዩ ልዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ቡድኑ ለሚንስቴሩ ማስረከቡን ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ ባላቸው አቅም ለመርዳት የሚፈልጉ በተለያየ ዓለም አገራት ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር ቡድኑ ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የሚያጋጥማትን ፈተና መሻገር የምትችለው የኢትዮጵያዊያን ንቁ ተሳትፎ ሲታከልበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያሉባት ብዙ ስብራቶች የሚጠገኑት በዜጎቿ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ በውጭ አገር ያሉ ዳያስፖራዎች ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚያደርጉትን አበርክቶ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።
ዓለም አቀፉ የዳያስፖራ የተግባር ቡድን እንደ አወሮፓውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 2022 እንደ ተቋቋመ መረጃዎች ያሳያሉ።