ቀጥታ፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሰራል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 3/2015 በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተቋም ደረጃ "የሕዳሴ ግድብ ቱር" መርኃ-ግብር በይፋ አስጀምሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭታቸውን የመለሱበት የአሁኑ ትውልድ የዘመን አሻራ ነው።

ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ስኬት ብርቱ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ሂደቱን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር ጥረት ቢያደርጉም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችና ወዳጆቿ የግንባታ ሂደቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተቋም ደረጃ ይፋ የተደረገው "የሕዳሴ ግድብ ቱር" ብሔራዊ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ኢትዮጵያዊያን በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ እንደሚያደርግ አንስተዋል።

ተቋሙ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚሰራው የዲፕሎማሲ ሥራ በተጨማሪ በውጭ የሚኖሩ ሚሲዮኖችና ኤምባሲዎች ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ብለዋል።  

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን ድኅነትን ለማሸነፍ በይቻላል መንፈስ የጀመረችው ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት። 

በቀጣይ በ36 ከተሞችና ከ200 በላይ ወረዳዎች የሚካሄደው "የህዳሴ ግድብ ቱር" መርሃ ግብርም ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚደረገውን የሃብት አሰባሰብ ሂደት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። 

ጽህፈት ቤቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ሕብረተሰቡ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል "የህዳሴ ግድብ ቱር" የጉዞ መርሃ-ግብር በትላንትናው ዕለት ማስጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም