የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ የሳውዲ አረቢያ አምባሳደር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ የሳውዲ አረቢያ አምባሳደር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 3/2015 የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ የሳውዲ አረቢያ አምባሳደር ዶክተር ፋሃድ አባይዳላህ አልሁማየዳኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ለሥራ ወደ ውጪ የሚሄዱ ዜጎች መብትና ደህንነታቸው የተጠበቀ እና የስምሪት ስርዓቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ውይይቱ ለሥራ ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚሄዱ ዜጎች መብትና ደህንነታቸው የተጠበቀ ማድረግ ላይ ያተኮረ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ የዜጎችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅና ሥራውም ከሰው ንክኪ የፀዳና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ ለሥራ ወደ ውጪ የሚሄዱ ዜጎችም ስለሚሄዱበት ሀገር በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ የቋንቋና ሙያዊ ሥልጠና መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የሥራ ስምሪቱ ትኩረት የሠለጠነና በከፊል የሠለጠነ የሰው ሃይል መላክ ላይ እንደሚሆን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያ የሳውዲ አረቢያ አምባሳደር ዶክተር ፋሃድ ኦባይዳላህ አልሁማየዳኒ በበኩላቸው “ሳውዲ አረቢያ ከዚህ ቀደም የነበረውን አሰራር በማሻሻል በርካታ ሠራተኞችን ከኢትዮጵያ ለመቀበል ዝግጅቷን አጠናቃለች” ብለዋል፡፡
ሳውዲ እየዘረጋች ያለው አዲስ የአሰራር ስርዓት ለሠራተኞች የቅጥርና የህክምና ዋስትናን ጨምሮ ደህንነታቸውን የሚያስጠብቅ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
የሥራ ስምሪት ስርዓቱ የተናበበ፣ ዘመናዊ፣ የተገልጋዮችን እንግልት እና ህገ ወጥነትን በሚቀንስ መልኩ በቅርቡ ተግባራዊ እንዲሆን በቅንጅት እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡