ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት ስራን ማጠናከር ለአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘላቂ መፍትሄ ነው - ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም

ድሬዳዋ ኢዜአ የካቲት 02 ቀን 2015፦የአረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋትን አጠናክሮ ማስቀጠል ለአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘላቂ መፍትሄ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ገለጹ።

የፌዴራል፣ የክልሎች እና የከተማ አስተዳድሮች የዘንድሮ በጀት አመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

May be an image of 2 people, people standing and indoor

ኮሚሽነሩ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያን የሚመጥን የአደጋ ስጋት አመራርን ዕውን ለማድረግ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር የተናበበና የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

የአረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋትን አጠናክሮ ማስቀጠል ለአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘላቂ መፍትሄ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ሁሉም አካል መርሃ ግብሮቹን ለማሳካት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ፍኖተ ካርታ፣ የህግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ፍሬያማ ስራዎች መሰራታቸውንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በአገሪቱ በግጭት፣ በድርቅና በጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ21 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ መደረጉንና ከፊሎቹ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተሰራው ስራ ከሳዑዲ አረቢያ ተመልሰው ወደየአካባቢያቸው የተሸኙ ወገኖችን የማቋቋምና ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዳይጋለጡ የማድረግ ስራ በተቀናጀ መንገድ መከናወኑንም ጠቁመዋል።

May be an image of 1 person and standing

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው አገር አቀፉ የግምገማ መድረክ ኢትዮጵያን የሚመጥን የአደጋ ስጋት አመራርን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩትን ተግባራትን ለማጎልበትና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያግዙ ምርጥ ተሞክሮዎች የሚቀስሙበት ይሆናል ብለዋል።

የአደጋ ቅነሳ የአካባቢ ልማት ዋና አካል ነው ያሉት ከንቲባው፤ አደጋን የመቀነስና የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት በመስጠት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ስራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው አገር አቀፍ የዕቅድ የስራ አፈፃፀም የሪፖርት ግምገማ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎና አባላት፤ የፌዴራል፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ ኮሚሽነሮችና አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም