ቀጥታ፡

ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት መገናኛ ብዙኃን የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 02/2015 ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማ ክንውን መገናኛ ብዙኃን የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠየቀ።

የኮሚሽኑን አስፈላጊነት፣ የምክክሩን ተግባራዊነት የሚያግዙ አዋጅና መመሪያዎች ዝግጅት ዙሪያ ከሕዝብና የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ተወካዮች ጋር ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ግብ ይዞ ወደ ሥራ ስለመግባቱ አብራርተዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የተለያዩ አገራት በምክክር ሂደት ምን አተረፉ? ምን ሳያሳኩ ቀሩ? እኛስ እንዴት መሄድ አለብን? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ዳሰሳ ተደርጓል ብለዋል።

ለምክክር ሂደቱ አዋጆችና መመሪያ ዝግጅት መደረጉንና ለምክክሩ መሳለጥ አጋዥ የሆኑ ጽህፈት ቤቶችን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማቋቋም ሂደት መጀመሩንም አንስተው ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ሂደት የመገናኛ ብዙኃን የነቃ ትብብርና ተሳትፎ የላቀ ሚና የሚኖረው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ስለ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቂ ግንዛቤና መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች የላቀ ሚና ያላቸው በመሆኑ የድርሻቸውን እንዲወጡ ፕሮፌሰር መስፍን ጠይቀዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ተወካይ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሙለታ፤ የአገራዊ ምክክሩ ስኬት በተለይም የሬዲዮ ጣቢያዎች በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃ ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብሏል።

ለዚህ ደግሞ ለሕብረተሰቡ ቅርብ የሆኑ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳ አድርገው እንዲሰሩበት ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ነው የገለጸው።

የከፋ ማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ተወካይ ጋዜጠኛ ተሾመ ኃይለሚካኤል በበኩሉ፤ ሕብረተሰቡን ለማስገንዘብ ጋዜጠኛው በቅድሚያ በቂ ግንዛቤ ሊጨብጥ ይገባል ሲል አመልክቶ ኮሚሽኑን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት ይኖርባቸዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ አሥር ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በዝግጅት ምዕራፉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም