የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከራስ አልፎ ለአካባቢው አገራት የልማት መሰረት የሚሆን ነው- የኢትዮጵያ ደን ልማት - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከራስ አልፎ ለአካባቢው አገራት የልማት መሰረት የሚሆን ነው- የኢትዮጵያ ደን ልማት

አዲስ አበባ የካቲት 02/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከራስ አልፎ ለአካባቢው አገራት ጥሩ ምሳሌና የልማት መሰረት የሚሆን ነው ሲል የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት 20 ሚሊዮን ዜጎችን በማሳተፍ ወደ 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከሏን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታውቋል፡፡

በተቋሙ የደን ልማት ዳይሬክተር ቢተው ሸዋአባው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ያለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ስኬታማና የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየር ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያም በጋራ የመልማት እሳቤ ባለፉት ዓመታት ለጎረቤት አገራት ችግኞችን የሰጠች መሆኑን አስታውሰውይህም ለቀጠናዊ ትብብር፣ ለልማት፣ በጋራ ለማደግ እና የጋራ መድረክ ለመፍጠር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ተሞክሮ ይዘው ቢሰሩ የደን ልማታቸውን ከፍ ለማድረግና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመከላከል ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጡበት እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
በተለይ በተደጋጋሚ በድርቅ ተጠቂ የሆኑ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ በመውሰድ ሊጠቀሙበት ይገባልም ሲሉ አክለው የተተከሉት ችግኞች የደን ሽፋንን ከፍ የሚያደርጉ፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን ለመታደግ የሚረዱ ናቸው ብለዋል።
እንዲሁም ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻርም ጉልህ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞች ባለቤት ኖሯቸው እንክብካቤ እንዲያገኙም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሰራቱንም ጠቁመው፤ በዚህ ወቅትም በእንክብካቤ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ለ5ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ግብ መያዙንም ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የሚተከለው 1 ቢሊየን የደን ችግኞች እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ደግሞ የጥምር ደን መሆናቸውን አስታውቀው በተለይም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለሚያስገኙ የችግኝ ዓይነቶች ሰፊ ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባከናወነችው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና ማግኘቷ ይታወቃል፡፡