የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል በሚገኙ ተጨማሪ ቅርንጫፎች የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል በሚገኙ ተጨማሪ ቅርንጫፎች የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
የካቲት 2/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በርካታ ተጨማሪ ቅርንጫፎች የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል በሽሬ፤ አክሱም፤ ዓድዋ፤ ሰለኽለኻ፤ ማይ ፀብሪ፤ እንዳባጉና፤ ውቕሮማራይ፤ ዓዲግራት፣ ውቕሮ፣ ፍረወይኒ፣ ሓውዜን፣ ዓዲጉዶም፣ ሒዋነ፣ ዓዲሽሁ፣ መኾኒ፣ ማይጨውና አካባቢው በሚገኙ በርካታ ቅርንጫፎች የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጿል።
ባንኩ አገልግሎት መስጠት በጀመረባቸው ቅርንጫፎች ለደንበኞች የተሟላ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጾ የባንኩ ደንበኛ የሆነ ማንኛውም ሰው በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የከፈተውን የሂሳብ ደብተር ይዞ በመቅረብ አገልግሎት ማግኘት ይችላል ብሏል፡፡
በተለያየ ምክንያት የሂሳብ ደብተራቸው የጠፋባቸው ደንበኞች ካሉ መታወቂያቸውን ይዘው በመቅረብ ባንኩ ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት በነበረ አሰራር መሰረት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም ባንኩ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቐለ ከተማ በሚገኙት ሁሉም ቅርንጫፎች እንዲሁም በዓብይ ዓዲ፤ ማይ ለሚን፤ ሳምረ፤ ግጀት፤ ሃይቂ መስሓል፤ወርቅ አምባ፤ አፅቢ እና አጉላዕ እና በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ቅርንጫፎች በትናንትናው ዕለት የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡