የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የቀጣናውን የደህንነት ችግሮች መመከት በሚያስችለው ቁመና ልክ እየተደራጀ ነው- ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የቀጣናውን የደህንነት ችግሮች መመከት በሚያስችለው ቁመና ልክ እየተደራጀ ነው- ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 02/2015 የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል በአፍሪካ ቀንድ ለሚከሰቱ ተገማች እና ኢ-ተገማች የጸጥታ እና ደህንነት ችግሮች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ተቋማዊ ቁመና እንዲኖረው የሚያስችል የመልሶ ማደራጀት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ሲሉ የተቋሙ ሊቀመንበር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ገለጹ።
31ኛው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የፖሊሲ አውጪ ሙያተኞች መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመክፈቻው ላይ የተገኙት በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር እና የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሊቀ መንበር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ፤ ውይይቱ ባለፈው ጥቅምት ወር በኬንያ ናይሮቢ ከተካሄደው የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተቋሙን አቅም በማሳደግ የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የአህጉሪቱን ሰላም እና ደህንነት በማስጠበቅ ድንበር ዘለል ወንጀሎችንና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የቀጠናውን ተገማችና ኢ-ተገማች የሰላም እና ፀጥታ ስጋቶችን ለመከላከል በሚያሰችለው ቁመና ልክ እንደገና እየተደራጀ ነው ብለዋል።
ለዚህም እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር መድረክ ተቋሙ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት እንዲኖረው በማድረግ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ዙሪያ የሚመክር ኃይል እንደሚደራጅ ተናግረዋል።
ተቋሙ በአፍሪካ ቀንድ አባል አገራት የሚከሰቱ ሰላምና ደህንነት ችግሮችን ምላሽ መስጠት የሚችል አንድ ተወርዋሪ ኃይል እንዲኖረው ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልጸው በመድረኩም የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ብቃትና ጥንካሬ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ አንስተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው ሽፈራው በበኩላቸው፤ ውይይቱ ተቋሙ ያለበትን የፖሊሲ ክፍተት ለመሙላት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖሊሲ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላም የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት እንደሚዘረጋ ተናግረዋል።
በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመከላከያ ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፤ የአፍሪካ ቀንድ በሰላምና ደህንነት እጦት ስጋት ላይ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ውይይቱ ቀጣናውን ከስጋት በዘላቂነት ለማላቀቅ የሚያስችል አቅጣጫና የመፍትሔ ሀሳብ ለማንሳትና ለመቀመር እንደሚያግዝ ይህንንም ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በማቀድ በፈረንጆቹ 2002 የተመሰረተ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ቡሩንዲ፣ ኮሞሮስ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሼልስ እና ኡጋንዳ ቋሚ አባል ሀገራት አሉት።
ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ደግሞ ደቡብ ሱዳን በታዛቢ ወይም ተጠባባቂ አባል ሀገርነት የተመዘገበች ሲሆን በቅርቡም ቋሚ አባል እንደምትሆን ይጠበቃል።