የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ያተኮረ የትምህርት ክፍል ለማቋቋም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ

158

አዲስ አበባ የካቲት 02/2015(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ያተኮረ የትምህርት ክፍል ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሌጁ በሁለንተናዊ የማኅበራዊ ሳይንስ ምርምር ላይ ያተኮረ ውይይት ከሚመለከታቸው የማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ጋር አድርጓል።

This image has an empty alt attribute; its file name is image-63.png

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደበበ ኤሮ ኮሌጁ በየዘመኑ ብዙ ለውጦችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው ሥር ያሉ ኮሌጆች የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራቸው ጊዜውን የሚመጥን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝና በተለያዩ ዘርፎች የማኅበረሰብ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።

የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ የትምህርት ክፍሎችን ይዞ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ያተኮረ አሥረኛ የትምህርት ክፍል ለማቋቋም ፕሮጀክት ተቀርጾ ዝግጅቶት መጀመሩን ተናግረዋል።

ወቅቱ ለትምህርቱ መጀመር አስገዳጅ መሆኑን ገልጸው፤ ከተቋማዊ ለውጥ ጋር አብሮ የሚሄድ ትምህርት መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመጀመር ከሚመለከታቸው ጋር መተማመን ላይ የተደረሰ ሲሆን ለተፈጻሚነቱም ኮሌጁ ዝግጁ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በዩኒቨርሲቲው የዘላቂ ልማት ግቦች አስተዳደር ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ በበኩላቸው፤ የፕሮጀክቱ ዓላማ በዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሳኩ ለመንግሥት እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲሁም የምርምር ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በማዕከል ደረጃ እየተቋቋመ መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ለስድስት ዓመታት የሚቆይና በቀጣይም የተቋም ቅርጽ ይዞ የሚቀጥል የምርምር ማዕከል እንደሚሆን አስረድተዋል።

በ2016 ዓ.ም. በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎችን መቀበል እንደሚጀምር የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና የአካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ደምስ መንግስቴ ናቸው።

በማዕከል ደረጃ ተቋቁሞ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ያተኮሩ የምርምር ፕሮጀክቶችን እንደሚደግፍ አመልክተው ለዚህም ኮሌጁ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት አድርጎ ማጠናቀቁን እና በቀጣይ ዓመት ተመራቂዎችን ማስተማር እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም