የስፖርት ቱሪዝም ለሀገር እድገትና ገፅታ ግንባታ ያለውን ሚና ለማጎልበት መንግስት እና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል

195

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 2/2015 የስፖርት ቱሪዝም ለሀገር እድገትና ገፅታ ግንባታ ያለውን ሚና ለማጎልበት መንግስት እና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያ ገለጹ።

ስፖርትና ቱሪዝም የማይነጣጠሉና ተመጋጋቢ ጉዳዮች ሲሆኑ የስፖርት ቱሪዝም የምንለውም ስፖርታዊ ክዋኔዎችን ለመታደምና ለመሳተፍ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ማዕከል ያደረገ ነው።

የስፖርት ቱሪዝም በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ የገቢ ምንጭ፣ የሀገር ገፅታ መገንቢያና የዲፕሎማሲ መሳሪያ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ለዚህም ነው ያደጉ የሚባሉ ሀገራት ከአነስተኛ የስፖርት ውድድሮች ጀምሮ እስከ ትልቁ የዓለም ዋንጫና የኦሎምፒክ ጨዋታ ድረስ የማዘጋጀት እድሉን ለማግኘት ብርቱ ፉክክር የሚያደርጉት።

ለአብነት ኳታር አስደናቂውን የ2022 የዓለም ዋንጫ የማዘጋጀት እድል እንዲሰጣት ብርቱ ጥረት አድርጋ አሸንፋለች።

ኳታር ይህን ሁሉ ዋጋ ከፍላ ውድድሩን ያዘጋጀችው በዋናነት የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባትና ከስፖርት ቱሪዝም ለመጠቀም ሲሆን በዚህም ለአንድ ወር በቆየው ውድድር እስከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚደርሱ ጎብኝዎችን ማስተናገዷ ተነግሯል።

ኢትዮጵያም በ10 ዓመት የልማት እቅዷ ውስጥ ስፖርት ለሀገራዊ፣ ማህበራዊ ልማት እና ብልጽግና እንዲውል ትኩረት ሰጥታለች።

በተለይም ስፖርትን ከባህልና ቱሪዝም ጋር አስተሳስሮ ለሀገር ገጽታ ግንባታ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና አንድነት ያለውን ፋይዳ ከፍ ለማድረግ ታቅዷል።

በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አስተዳደርና የቢዝነስ ተመራማሪ ዶክተር ጋሻው አብዛ፤ በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ቢኖርም ገና ያልተነካ ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ቅርሶችና የተፈጥሮ ፀጋ የተቸረች ሀገር እንደመሆኗ ጸጋዎቿን አልምታ የቱሪዝም ገቢዋን ለማሳድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗን አድንቀው፤ ከስፖርት ቱሪዝም አንጻር ግን ብዙ ይቀራል ባይ ናቸው።

የስፖርት ቱሪዝሙ በስፋት ከተሰራበት ለሀገሪቱ ዓመታዊ ጥቅል ምርት መጠን(GDP) የራሱን ሚና የሚያበረከት ዘርፍ መሆኑን በማንሳት።

ኢትዮጵያውያን አስደናቂ ታሪክ ያስመዘገቡበት አትሌቲክስ ለሀገሪቱ የስፖርት ቱሪዝም ትልቅ ዕድል እንዳለው ተናግረዋል።

ምቹ የማዘውተሪያ ቦታ በመገንባት የውጭ ሀገር አትሌቶችን ወደ ሀገሪቱ በመጋበዝ ከታዋቂ አትሌቶች ጋር የሩጫና የልምምድ መድረኮች በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ ጎብኝዎችን መሳብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ይህም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴል እንዲሁም በአስጎብኚነት ለተሰማሩ ዜጎች ከፍተኛ ጥቅም እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።

በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ታሪክ በሰሩ ኢትዮጵያውያን ስም ሙዚየም በመገንባት የገቢ ምንጭ መፍጠር እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ከግል ተቋማት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ ሀገርን ተጠቃሚ በማድረግ በአርዓያነት እንደሚጠቀስ ያነሱት ዶክተር ጋሻው፤ ሌሎች ባለሀብቶችም ዘርፉን ለማጎልበት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

መንግስትም ኢትዮጵያ ከስፖርት ቱሪዝም በረጅም ጊዜ ተጠቃሚ የምትሆንበትንና ለእድገትና ገፅታ ግንባታ ቁልፍ መሳሪያ የምታደርግበትን ምቹ አውድ መፍጠር እንዳለበት ተናግረዋል።

ለዚህም ልዩ ስትራቴጂ ቀይሶ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም