ሁለት የትራፊክ ፖሊስ አባላት ወድቆ የተገኘን 55 ሺህ ብር ለባለቤቱ አስረከቡ

201

ሀረር (ኢዜአ) የካቲት 02 ቀን 2015 በሀረር ከተማ ወድቆ የተገኘን 55 ሺህ ብር ሁለት የትራፊክ ፖሊስ አባላት ለባለቤቱ ማስረከባቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ብሩን አግኝተው ለባለቤቱ ያስረከቡት በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በትራፊክ ሙያ በማገልገል ላይ የሚገኙት ዋና ሳጅን ሳምራዊት ሚልዮን እና ረዳት ኢንስፔክተር ሚስራ አብዲ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

አባላቱን ብሩን ያገኙት በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት እንደነበርም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘካሪያ እንደገለጹት፤ ብሩ መንገድ ላይ በፌስታል ተጠቅልሎ ልጆች በእግር ሲመቱት መበተኑን የትራፊክ አባላቱ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ብሩን ሰብስበውም ባለቤቱ እስኪገኝ ወደ መምሪያ አምጥተው ማስረከባቸውን ገልጸው፤ የትራፊክ ፖሊስ አባላቱ ማህበረሰቡን በቅንነት ለማገልገልና ደህንነቱን ለመጠበቅ ምንግዜም ዝግጁ መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የፖሊስነት ሙያ ዋና ዓላማ የህዝብን ደህንነት ብሎም ንብረትን መጠበቅ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነር ነስሪ፤ ወድቆ የተገኘው 55 ሺህ ብሩ ባለቤቱ እስኪገኙ ድረስ እዚያው መምሪያ መቆየቱን ተናግረዋል።

የብሩ ባለንብረት የሆኑት በክልሉ የሶፊ ወረዳ ነዋሪና የ3 ልጆች እናት ወይዘሮ ፋጡማ ኡስማን እንደተናገሩት፤ ሦስት ልጆቻቸውን ያለ ረዳት እያሳደጉ አንደሚገኙ ጠቁመው፤ በከተማው አትክልት ሽጠው ሲመለሱ ብሩ እንደጠፋባቸው ገልፀዋል፡፡

ብሩ በጠፋባቸው ወቅት ማዘናቸውን የገለፁት ወይዘሮ ፋጡማ፤ ብሩን መልሰው የማግኘት ተስፋ እንዳልነበራቸው ተናግረው፤ በትራፊክ ፖሊስ አባላት ብሩ ተገኝቶ በመረከባቸው ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል፡፡

የጠፋውን ብር ባለቤቱን አረጋግጠው ብሩን ለባለቤቱ አንዲመለስ ያደረጉት የትራፊክ ፖሊስ አባላት ከኮሚሽኑ የክብር ሰርተፍኬት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ በቀጣይም ለሠሩት ሥራ የሚመጥን ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም