ቢሮው በምዕራብ አርሲ ዞን ለሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

70

ሻሸመኔ /ኢዜአ/ የካቲት 2/2015 --የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ቢሮ በምዕራብ አርሲ ዞን ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የአልባሳት፣ የምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲንቢርቱ እንደገለጹት ቢሮው በዞኑ ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች የምግብ፣ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያካተተ ድጋፍ አደርጓል።

ድጋፉ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው መሆኑን ገልጸው ከተለያዩ በጎ አድራጎት፣ መንግስት ተቋማትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተሰበሰበ እንደሆነም ተናግረዋል።

የህግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የተለያዩ ሙያንና እውቀትን የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበው በተለይ ሴቶችና ህጻናት በሙያና በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ከክልሉ ማረሚያ ቤቶች ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።

የምዕራብ አርሲ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተወካይ ኃላፊ ኮማንደር ቶለሳ ኢዳኦ በበኩላቸው የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ለህግ ታራሚዎች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የህግ ታራሚዎች የስብአዊ መብታቸው ተጠብቆ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የተለያዮ ሙያዎችን እየቀሰሙ መሆኑን በማውሳት የመንግስት ተቋማት፣ ባለ ሃብቶችና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለህግ ታራሚዎች የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም