ሩሲያ ለአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

158

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 2/2015 ሩሲያ ለአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች።

የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ጋር ተወያይተዋል።።

አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አካዳሚው የመንግስትንና የግል ተቋማትን አመራሮች እያሰለጠነ እንደሚገኝ እና ይህንንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተቋማዊ ማሻሻያ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ምህረት ተናግረዋል።

ከተቋማዊ ሪፎርሙ በኋላ አካዳሚው ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው በርካታ አገር አቀፍና አህጉር አቀፍ ፕሮግራሞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ይህንንም ለማሳካት ተቋሙ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ስትራቴጂያዊ አጋርነትን በመመስረት የአካዳሚውን ተልዕኮ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አካዳሚው ከሩሲያ ጋር በስልጠና እና በምርምር መስኮች በትብብር በመስራት የተቋሙን የአፈጻጸም አቅም ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለውም ነው ዶክተር ምህረት ያመለከቱት።

በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች በትብብር ስለሚሰራባቸው መስኮች የሀሳብ ልውውጥ እንደሚኖር መናገራቸውን ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም