"የሕዳሴ ግድብ ቱር" የሚል ስያሜ ያለው የጉዞ መርሐግብር ተጀመረ

156

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 2/2015 ሕብረተሰቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለውን አጋርነት የማጠናከር እና ገቢ የማሰባሰብ አላማ ያለው "ሕዳሴ ግድብ ቱር" የተሰኘ የጉዞ መርሐግብር ዛሬ ተጀምሯል።

ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደውን መርሐግብር የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት በጋራ በመተባበር እንዳዘጋጁት ተገልጿል።

የጉዞ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎችም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ሽኝት ተደርጎላቸዋል ፡፡

ከአንድ ወር በላይ ይቆያል የተባለው "የሕዳሴ ግድብ ቱር" በ50 የክልል ከተሞችና ሌሎች ወረዳዎች እንደሚከናወን ተነግሯል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያውያን ተባብረን መገደብ እንደጀመርነው ድጋፋችንንም አጠናክረን መቀጠል ይገባናል ብለዋል።

የተለያዩ የልማት ስራዎችን በአንድነት በትብብር ከሰራን ኢትዮጵያ የማታድግበት ምንም ምክንያት የለም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ታሪክ ባህል እና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አምሀ አለሙ በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ በሚካሄደው ጉዞ እስከ 200 ሚሊዮን ብር በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮች ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም