ከውጭ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ኬብሎችንና ትራንስፎርመሮችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በቅንጅት እየተሰራ ነው

78

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 ከውጭ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ኬብሎችንና ትራንስፎርመሮችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደተናገሩት ፤ በአሁኑ ወቅት ለኢንዱስትሪዎች 68 ሺህ ኪሎ ዋት ኃይል እየቀረበ ነው።

ይህንንም ወደ 255 ሺህ ኪሎ ዋት ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኬብሎችንና ትራንስፎርመሮችን በበቂ ሁኔታ በማምረት በአገር ውስጥ የመተካት ሥራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ለአዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም ሆነ ለነባሮች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ትራንስፎርመር፣ ኬብሎችን እና የትራንስፎርመር መለዋወጫዎችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በቁጥር መጨመራቸውንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ሲዓ፤ በኢንዱስትሪዎች አካባቢ ያለውን የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት የመሰረተ-ልማትና የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት በትብብር ይሰራል ብለዋል።

ለኢንዱስትሪዎች ከመደበኛው የኃይል ማሰራጫ የተለየ መስመር በመዘርጋት የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የታቀደ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም በኃይል መሰረተ-ልማት ግንባታና በግብዓት አቅርቦት ላይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቀጣይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም