የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቀቀ

66

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 1/2015 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፕሪሚየር ሊጉ መሪነት ይዟል።

በድሬዳዋ ከተማ ከአምስተኛ እስከ ዘጠነኛ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የሊጉ መርሐግብር ዛሬ ተቋጭቷል።

በድሬዳዋ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ባህር ዳር ከነማ ፌደራል ማረሚያን 37 ለ 33 አሸንፏል።

ውጤቱንም ተከትሎ ባህር ዳር ከነማ ነጥቡን ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቋል።

በአንጻሩ ፌደራል ማረሚያ በአምስት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ውድድር በሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ16 ነጥብ ይመራል።

መቻል በ14 እንዲሁም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ11 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻው ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በዘንድሮ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠኝ ክለቦች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም