የፀማይ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል “ባርባይሳ” እየተከበረ ነው

178

ጂንካ የካቲት 1 ቀን 2015 (ኢዜአ) የፀማይ ህዝብ የዘመን መለወጫ የ“ባርባይሳ” ክብረ በዓል በደቡብ ኦሞ ዞን በበና ፀማይ ወረዳ ሉቃ ቀበሌ በድምቀት እየተከበረ ነው።

የፀማይ ህዝብ የዘመን መለወጫ “ባርባይሳ” በየአመቱ የካቲት 1 በተለያዩ ባህላዊ ስነስርአቶች እየተከበረ ይገኛል።

በክብረ በአሉ ላይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የክልሉ ሴቶች ሊግ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ወላይቴ ቢቶና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳን ጨምሮ የዞኑ አመራሮች፣ የባህል መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የፀማይ ህዝብ አባላትም በበአሉ ላይ ታድመዋል።

የ”ባርባይሳ" በዓል የዘር እህል ተባርኮ የሚሰጥበትና የበልግ እርሻ ዘር የሚዘራበት እንዲሁም አካባቢው ሰላም እንዲሆን፣ ቂምና ቁርሾ እንዲወገድ ለፈጣሪ ጸሎትና ምስጋና የሚደረግበት መሆኑ ተመላክቷል ።

እንዲሁም በሽታ ከአገር እንዲጠፋ፣ጎተራ እንዲሞላና ከብቶች ጋጣ እንዲሞሉ የሚመርቅበትና ወደ ፈጣሪ ተማፅኖ የሚደረግበት ክብረ በዓል እንደሆነም ተገልጿል ።

በዓሉ በህዝቦች ዘንድ ሰላምና አንድነት እንዲሁም ተስፋና ልምላሜን በማሳየት ለበለጠ ውጤታማነት መነሳሳትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ባህላዊ ክንዋኔዎች የሚታዩበት እንደሆነም በስነ ስርአቱ ላይ ተመላክቷል ።

በበዓሉ ላይ የጸማይ ህዝብ ባህላዊ ጭፈራዎች፣ ምግቦችና ባህላዊ ቁሳቁሶች ለታዳሚያን ዕይታ እየቀረቡ ይገኛሉ።

በአሉ ታዳሚዎችን በመመረቅና የበልግ እርሻ ዘር ተባርኮ ወደስራ እንዲገቡ እወጃ ከተነገረ በኃላ እንደሚጠናቀቅ ተመላክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም