ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ሰባት ወራት በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓት ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ሰባት ወራት በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓት ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት ከ37 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ምርት ገበያው ባለፉት ሰባት ወራት በቢሊዮን ብር በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ፈፅሟል።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ የተፈጸመው ገዢዎች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመግዣ አካውንቶች ገንዘብ ገቢ የሚያደርጉበትና በምርት ገበያው አማካኝነት ለሻጮች የሚከፈልበትን አሰራር በመዘርጋት መሆኑንም አብራርተዋል።

የምርት ገበያውን የግብይት ስርዓት ለማዘመን ከ15 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ዳሽን ባንክ ጋር የውል ስምምነት በመግባት ሲሰራ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ ምርት ገበያው ከ19 ባንኮች ጋር ስምምነት በማድረግ በግብይት ሂደቱ ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት እንዲስፋፋ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ከአርሶ አደሩ እስከ አቅራቢው፤ ከምርት ላኪዎች እስከ ተቀባዮች ባለው የገበያ ሰንሰለት የሚያልፉ ተዋንያን የሚሳተፉበት መሆኑንም የኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ይሄም የምርት ገበያው ተዋናዮች በዘመናዊ የግብይት ስርዓት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።

የግብይት ስርዓቱ አቅራቢዎች ወይም አምራቾች የሸጡበትን ገንዘብ ከገዢው የባንክ ሂሳብ በፍጥነት በማስተላለፍ የግብይት ስርዓቱን የሚያፋጥን የሀገርን ኢኮኖሚም የሚያሳድግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባለፊት ሰባት ወራት በምርት ገበያው አማካኝነት በኤሌክትሮኒክስ ግብይት የተከፈለው የገንዘብ መጠን 14 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የክፍያ አገልግሎቱ የሚከናወነው በምርት አቅራቢዎች እና ገዢዎች በተከፈቱ ከ11 ሺህ በላይ የባንክ አካውንቶች አማካኝነት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት ወደ ምርት ገበያው የመግዣ አካውንቶች ከገዢዎች ለግብይት የገባውና ለሻጮችም በምርት ገበያው አማካኝነት የተከፈለው የገንዘብ መጠን ከ350 ቢሊየን ብር በላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም