ቀጥታ፡

በአርሲ ዞን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ለማሳካት ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለኢንቨስትመንት መዘጋጀቱ ተገለጸ

አሰላ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 በአርሲ ዞን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ለማሳካት ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚውል መሬት መዘጋጀቱን የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የ'ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ' በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ በዞኑ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮች በተገኙበት ተካሄዷል። 

የአርሲ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበበ አሰፋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በዞኑ ንቅናቄውን ለማሳካት ለሰፋፊ እርሻዎች፣ ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችና ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚውል ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። 

ለዚህም ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ እንተርፕራይዞችንና ባለሃብቶችን ለመደገፍ ንቅናቄው ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች እና ተቋማት ላይ ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን ጠቁመዋል። 

በአሰላ ከተማ 68 ለሚሆኑ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ እንተርፕራይዞች 150 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማስተላለፋቸውን የገለጹት ደግሞ የአሰላ ከተማ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ረዒሳ አደም ናቸው። 

በተጨማሪም የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሰራው ስራ የትራንፎርመር፣ የውሃና የመንገድ አግልግሎት ተደራሽ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአርሲ ዞን አስተዳደሪ አቶ ሙሳ ፉሮ በበኩላቸው በዞኑ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ለማሳካት ከባለሃብቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

በዚህም የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና ተያያዥ ችግሮች ለመቅረፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮ ዓመት 546 የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ገልጸዋል።

በእስከ አሁኑ ሂደት ከ100 በላይ የሚሆኑ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን የገለጹት አቶ ሙሳ የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች የባለሃብቶችንና የእንተርፕራይዞችን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ንቅናቄውን ለማሳካት የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል። 

በተጨማሪም የፈጣን አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን ለአልሚ ባለሃብቶች ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ተወካይ አቶ ሸለመ በቀለ በበኩላቸው ንቅናቄውን ለማሳካት የመሬት አቅርቦት፣ የብድር አገልግሎትና ለባለሃብቶችና ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዘላቂና ወጥነት ያለው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህም ከ600 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በዘንድሮ ዓመት ተጠናቀው ወደ ማምረት እንደሚገቡ ጠቅሰው ስራ ያቆሙ ከ100 በላይ የማኑፋክቸሪንግ እንዱስትሪዎች በንቅናቄው በተደረገላቸው ድጋፍ ዳግም ወደ ምርት መመለሳቸውን ገልጸዋል። 

በፈሳሽ የአፈር ማዳባሪያ ማምረት ዘርፍ ላይ የተሰማሩት አቶ መላኩ ፀጋ በበኩላቸው ምርቱን በብዛት፣ በጥራትና በተፈለገው ጊዜ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ የማስፋፊያ መሬት ያስፈልገናል ብለዋል። 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሃጂ አደም ኢብሮ እንዲሁ ምንም ልማት ሳይሰራባቸው ታጥረው የተቀመጡ የእርሻና የኢንዱስትሪ መሬቶች ለአልሚ ባለሃብቶች መሰጠት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም