በሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የጀመሩት ሁለት ዩኒቶች የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 9 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ ይዘዋል - የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
በሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የጀመሩት ሁለት ዩኒቶች የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 9 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ ይዘዋል - የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ሁለት ዩኒቶች የአገሪቷን አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 9 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት ለሱዳንና ጅቡቲ ለሽያጭ ካቀረበችው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ32 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷንም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 9 ሺህ 543 ጊጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት አቅዶ የእቅዱን 87 በመቶ ማሳካት ተችሏል።
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንዳለው አመልክተዋል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 18 ሺህ 994 ጊጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት እቅድ መያዙን ገልጸዋል።
በስድስት ወራቱ ፊንጫ፣አዋሽ ሶስተኛ፣ጢስ ዓባይ ሁለተኛ እንዲሁም አዳማ አንድና ሁለት የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ከተያዘላቸው እቅድ በላይ ማመንጨታቸው ነው የተነገረው።
የኢትዮጵያ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሆነው ጊቤ ሶስት ከአጠቃላይ የኃይል አቅርቦቱ 34 ነጥብ 8 በመቶ ድርሻ እንዳለውም ተጠቁሟል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች ደግሞ በስድስት ወራት ከጥቅሉ የኃይል ምንጭ የጥቅሉን 9 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ አበርክተዋል ነው ያሉት አቶ ሞገስ።
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ወደ ሱዳን እና ጅቡቲ 38 ነጥብ 23 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 32 ነጥብ 61 ሚሊየን ዶላር ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
ለመላክ ከታቀደው ኃይል 85 በመቶው ተልኳል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደገና መጀመሩንም የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አክለዋል።
በኢትዮጵያ 96 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው ከውሃ ሲሆን እንደሆነና ቀሪው ደግሞ ከነፋስ ኃይል እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።