ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሌማት ቱሩፋትን ውጤታማ ለማድረግ የእንስሳት ሀብትን በምርምር ለመደገፍ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሌማት ቱሩፋትን ውጤታማ ለማድረግ የእንስሳት ሀብትን በምርምር ለመደገፍ እየሰራ ነው

ሚዛን አማን(ኢዜአ) የካቲት 1/2015-ለሀገራዊ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ውጤታማነት የእንስሳት ሀብት ልማት ሥራን በምርምር ለመደገፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዮት አስረስ እንዳሉት፣ የእንስሳት ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በተለይ አርሶና አርብቶ አደሩ ከእንስሳት ሀብቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።
እንደ ሀገር የተጀመረውን የሌማት ቱሩፋት መርሃግብር ውጤታማ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በእንስሳት ሀብትና መሰል ዘርፎች ምርምር እያካሄደ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ውጤቶቹን አርሶና አርብቶ አደሩ እንዲጠቀምባቸው በማገዝ ላይ መሆኑን አስረድተው የእንስሳት ማዳቀል ሥራውን ከቤንች ሸኮ ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተለያየ ዙር እንስሳትን የማዳቀል አገልግሎት እንደሚሰጥ የገለጹት ዶክተር አብዮት፣ "ከትናንት ጀምሮለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለ ዘመቻም ከ114 በላይ ላሞችን ለማዳቀል ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል" ብለዋል።
አርሶና አርብቶ አደሩ በሌማት ቱሩፋት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተደገፉ ሥራዎችን በማቅረብ የማለማመድ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ዶክተር አብዮት እንዳሉት እንደ ሀገር ከፍተኛ የወተት ሀብት ለማግኘት የሚያስችል የእንስሳት ሀብት ቢኖርም የተሻሻሉና ምርጥ ዘር ባለመሆናቸው ተገቢ ጥቅም እየተገኘ አይደለም።
ዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉና በምርምር የሚገኙ የተለያዩ ምርጥ የላም ዝርያዎችን በግቢው ውስጥ በማላመድ ለአርሶ አደሮች እንደሚያከፋፍልም ዶክተር አብዮት ገልጸዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ የእንስሳት ጤና ባለሙያ አቶ ላቀው ዓለሙ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ለዞኑ አርሶ አደሮች እየቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተዳቀሉ ያሉ ምርጥ ዘር ላሞች በቀን ከ20 እስከ 30 ሊትር ወተት እንደሚሰጡ ጠቁመው፣ በእዚህም አርሶ አደሮችን የተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።
"አርሶ አደሩ እንስሳትን ወደ ማዳቀያ ቦታ ከማምጣት ጀምሮ ለላሞች አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥንቃቄ በማድረግ ለውጤታማነቱ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።

በሚዛን አማን ከተማ የአማን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኤፍሬም ጃሊ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ላም በቀን የሚያገኘው ወተት ከ1 ሊትር ተኩል እንደማይበልጥ ገልጾ፣ በማዳቀል በቀጣይ የተሻለ የወተት ምርት መስጠት የምትችል ላም አገኛለሁ ብሎ ተስፋ ማድረጉን ገልጿል።