የአደረጃጀት ጥያቄ ምላሽ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ይበልጥ ያጠናክራል -ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው

58

ሀዋሳ የካቲት 1/2015(ኢዜአ) አገልግሎቶችንና የመልማት ፍላጎትን መነሻ በማድረግ እየተከናወነ ያለው የአደረጃጀት ምላሽ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ይበልጥ ያጠናክራል ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

የደቡብ ክልል የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የበጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ ጀምሯል።

በመክፈቻው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት መንግስት ለረጂም ጊዜያት ሲነሳ የቆየን የአደረጃጀት ጥያቄ በመቀበል ደረጃ በደረጃ እየመለሰ ነው።

በዚህ ሳምንት በክልሉ የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የአደረጃጀት ጥያቄዎች ምላሽ አገልግሎትን በቅርበት ለማግኘትና የመልማት ሂደትን ለማሳለጥ መሆኑን ገልጸው ይህም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።

በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት እየጎለበተ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነም ጠቁመዋል።

መንግስት ሰላማዊ፣ አሳታፊና ግልጽ አሰራሮችን በመከተል ለህዝቦች ጥያቄ የሚሰጠውን ምላሽ እየተከናወኑ ካሉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ጋር በማስተሳሰር፣ አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ከመፈጸም አኳያ የፊት አመራሩ ሀላፊነቱ የበለጠ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በልማት ሥራዎች በግማሽ ዓመቱ ከተመዘገበው መልካም ተሞክሮን በመቀመርና ከክፍተቱ ትምህርት በመውሰድ አሻጋሪ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል ውይይት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የፕላንና ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ባዩሽ ተስፋዬ የክልሉን የአስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች አጠቃላይ ሪፖርት አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም