የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ከፈረንሳይ መንግስት ግምጃ ቤት የበላይ ሀላፊ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ከፈረንሳይ መንግስት ግምጃ ቤት የበላይ ሀላፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ከፈረንሳይ መንግስት ግምጃ ቤት የበላይ ሀላፊ ሚስተር ኢማኑኤል ሞሊን ጋር መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
የዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፈረንሳይ ካደርጉት የስራ ጉብኝት በተጓዳኝ የተካሄደ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ዶክተር ኢዮብ ከፈረንሳይ መንግስት ግምጃ ቤት የበላይ ሀላፊ ከሚስተር ኢማኑኤል ሞሊን ጋር በሁለቱ ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ ትብብር ላይ ፍሪያማ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ወቅት ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች እያከናወነች ስላለችው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ማብራሪያ መስተጣቸውም ተመላክቷል፡፡
በማብራሪያቸውም በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን መልሶ የማቋቋም ሂደቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
ውይይቱ ፈረንሳይ በሁለትዮሽና በብዙሀን የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው የልማት ድጋፍ ላይ ያተኮረ እንደነበርም ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፈረንሳይ በበለጸጉ 20 ሀገራት ማእቀፍ መሰረት የኢትዮጵያ የብድር ጫና የሚቃለልበትን ሂደት ለማፋጠን ፈረንሳይ ቁርጠኛ መሆኗ በውይይቱ መነሳቱም ተመልክቷል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ መገኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል፡፡