በምዕራብ አርሲ ዞን ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እየተዘጋጀ ነው

ሻሸመኔ (ኢዜአ) የካቲት 01/2015 በምዕራብ አርሲ ዞን ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ ጥበቃ ስራ ሂደት መሪ አቶ ኡመር ኤጀሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኞቹ ድርቅን በመቋቋምና እርጥበትን በማቆየት ምርታማነትን የሚጨምሩ ዝርያዎች ናቸው።

በዚህ ዓመት ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዞኑ በበጋው ወቅት የክረምቱን ውሃ ለመያዝ የሚያስችሉ የእርከን፣ የጉድጓድና ሌሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፤ የችግኝ ተከላው መርሃ-ግብር ከሚያዝያ ወር ጀምሮ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

እየተዘጋጁ ያሉ ችግኞች የአፈር ለምነትን የሚጨምሩና ለከብቶች መኖ የሚያገለግሉ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸው ሆነው ይህም ድርቅን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አንዱ አካል ነው ብለዋል።

ችግኞች እየተዘጋጁ ያሉት በዞኑ በሚገኙ 3 ሺህ 225 የችግኝ ጣቢያዎችና በአርሶ አደሮች አማካኝነት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተለይም እንደ ዋርካ፣ ጥድ፣ ቀርከሃ፣ ዝግባ፣ ጥቁር እንጨትና ሌሎች የሀገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች መሆናቸውንም አክለዋል።

ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በዞኑ ከተተከሉ ከ146 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ በተደረገው ጥረት 85 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ገልጸዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር አስፈላጊውን አገልግሎት እስኪሰጡ ድረስ እንክብካቤ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም