ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር ለምነት እንዲመለስና የደረቁ ምንጮች እንዲያገግሙ አስችሏል--የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

106

ባህርዳር (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር ለምነት እንዲመለስና የደረቁ ምንጮች እንዲያገግሙ ከማድረግም ባለፈ አርሶ አደሩ ለእንስሳቱ በቂ መኖ እንዲያገኝ አስችለዋል ሲል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በአማራ ክልል የዘንድሮው የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በጥራት እያከናወነ መሆኑን ቢሮው ገልጿል። 

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የህልውና ጉዳይ ሆኖ እየተሰራ ነው። 

በክልሉ ዘንድሮ ከ310 ሺህ ሄክታር በላይ የግልና የወል መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በአርሶ አደሩ ተሳትፎ ለማከናወን ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 

የልማት ስራው በክልሉ በአብዛኞቹ ዞኖች ከእዚህ ወር አጋማሽ ጀምሮ እየተከናወነ ሲሆን፤ እስካሁን ከ60 ሺህ 830 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ማከናወን ተችሏል ብለዋል። 

በዘንድሮው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ እንደሚሳተፍ ጠቅሰው እስካሁን ከዕቅዱ 67 በመቶ የሚሆነው እየተሳተፈ መሆኑን አመልክተዋል። 

እንደ አቶ እስመለዓለም ገለጻ ሰብል ተሰብስቦ ባልተጠናቀቀባቸው የምስራቅ ጎጃምና የሰሜን ሸዋ ዞን ደጋማ ወረዳዎች ሥራው በዚህ ሳምንት እንደሚጀመር ይጠበቃል።

በክልሉ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ዘላቂነት እንዲኖረውም ከልማት ስራው ጎን ለጎን 256 የተፋሰስ ልማት ህብረት ስራ ማህበራት መቋቋማቸውን አስረድተዋል። 

ማህበራቱ ተፋሰሱን በባለቤትነት በመጠበቅና በመንከባከብ የለም አፈር መሸርሸርን በመቀነስ ለምነቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማድረግ በኩል የላቀ ፋይዳ እንደሚኖራቸው አብራርተዋል። 

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር ለምነት እንዲመለስና የደረቁ ምንጮች መልሰው እንዲመነጩ ከማድረግም ባለፈ አርሶ አደሩ ለእንስሳቱ በቂ መኖ እንዲያገኝ አስችለዋል ብለዋል።  

የዘንድሮው የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ እስከ መጪው ወር መጨረሻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። 

በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ አርሶ አደር ሰውመሆን አበበ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ከመጀመሩ በፊት በክረምት ወቅት ለም የሆነው አፈር በጎርፍ ይወሰድ እንደነበር አስታውሰዋል።  

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራን ትኩረት ሰጥተው መስራት ከጀመሩ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ የአፈር ለምነቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ በአንድ ሄክታር እስከ 2 ኩንታል የምርት ጭማሪ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

''የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እያስገኘ ያለውን ጥቅም እየተረዳን በመምጣታችን በዘንድሮው ዓመት በበጋ ወራት የጀመርነውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እያከናወን እንገኛለን'' ብለዋል።  

''የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራን ማከናወን የሚያስገኘው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው'' ያሉት ደግሞ በባህር  ዳር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ዋለ ደሞዝ ናቸው። 

በአካባቢያቸው ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የተከናወነባቸው የአቁራ፣ የተራራና የታብሊ ተፋሰሶች ዋነኛ የእንስሳት መኖ መገኛ ምንጭ ሆነው እያገለገሉ መሆኑን ተናግረዋል።  

ዘንድሮም ''የግሊት'' ጎጥ ተፋሰስን ለማልማት የአካባቢው አርሶ አደር የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ያለቀስቃሽ በራሱ ተነሳሽነት እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል። 

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከ7 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን አብዛኛው በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም