በምርት ዘመኑ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በምርት ዘመኑ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ
ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በ2014/15 ምርት ዘመኑ በአኩሪ አተር ከተሸፈነው 340 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት የአኩሪ አተር ሰብል ልማትና ግብይት ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሂዷል፡፡
በሚኒስቴሩ የእርሻና 'ሆርቲካልቸር' ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ ለውጪ ገበያም ሆነ ለአምራች አንዱስትሪው ግብአት የሚውል አኩሪ አተር በበቂ መጠን ማምረት የሚያስችል ምቹ ስነ-ምህዳር አለ፡፡
ለአኩሪ አተር ልማት ምቹ ስነ-ምህዳር ካላቸው አካባቢዎች መካከልም አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቢኒሻንጉል፣ ደቡብና ጋምቤላ ክልሎች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሀገር ደረጃ በምርት ዘመኑ በአኩሪ አተር የለማው 340 ሺህ ሄክታር መሬት መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህም ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል ብለዋል።
በዚህ ዓመት የተሻለ ምርት ማግኘት ቢቻልም የተደራጀ የገበያ ሥርዓት ያለመፈጠር እንዲሁም በሥራ ላይ ያሉት የህግ ማእቀፎች፣ አዋጆችና ፖሊሲዎች ምቹ ያለመሆን አምራቹን ቀጥተኛ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች ያሉባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአኩሪ አተርን የገበያ ችግር በመፍታት በኩል የአምራችና የምርት ተጠቃሚውን ግንኙነት የሚወስን 'ኮንትራት ፋርሚንግ' ሥርዓት ለማበጀት የሚያስችል የውል ስምምነት አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራትን ልምዶች በመቀመር የተዘጋጀ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ከሁለት ወር በኋላ ጸድቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
አዋጁ የአኩሪ አተር የገበያ ችግርን በመቅረፍ በኩል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም አብራርተዋል፡፡
በአማራ ክልል በ2014/15 ምርት ዘመን ከ248 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአኩሪ አተር በመሸፈን ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መመረቱን የተናገሩት ድግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው ናቸው፡፡
በክልሉ አሁንም አርሶ አደሩ ላመረተው ምርት ሰፊ የገበያ መዳረሻ ከማመቻቸት ጀምሮ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የቅባት ሰብሎችን እሴት ጨምረው የሚያመርቱ ባላሀብቶችና ኩባንያዎች የአርሶ አደሩን ምርት በስፋት በመረከብ የገበያ ችግሩን ለቅረፍ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ ከአዊ ዞን የመጡት አርሶ አደር ሽታ ሰውነት እንደተናገሩት፤ በምርት ዘመኑ በ10 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት አኩሪ አተር 200 ኩንታል ምርት ቢያገኙም በገበያ ችግር ምርቱን እስካሁን እንዳልሸጡ ተናግረዋል፡፡
አምና አንድ ኩንታል አኩሪ አተር እስከ 4 ሺህ ብር መሸጣቸውን አስታውሰው፤ ዘንድሮ ግን አንድ ኩንታል ወደ 3 ሺህ 400 ብር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
በቡሬ ግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአኩሪ አተር ምርት ላይ እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርበው 'ሪች ላንድ' ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተወካይ አቶ ዳዊት አውደው በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በዚህ ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል አኩሪ አተር ከአርሶ አደሩ ለመግዛት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ የአኩሪ አተር አምራች አርሶ አደሮች፣ የእርሻ ባለሀብቶች፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ምርምር ላይ የሚሠሩ ማእከላት እንዲሁም የፌዴራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡