ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ867 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ867 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 ባለፋት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ867 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብስቡን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኝነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሕዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርገው አስተዋጽዖ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አንስተው በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያው ስድስት ወራት 1 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን ከ867 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።
’የተሰበሰበው ገንዘብ ከዳያስፖራው፣ ከአገር ውስጥ የቦንድ ግዥና ስጦታና እንዲሁም ከ8100 A አጭር የጽሁፍ መልዕክት የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ደግሞ የቦንድ ግዥና ስጦታ ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ ትልቁን ሥፍራ ይዘዋል ብለዋል።
ሕብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበው ጽህፈት ቤቱ አዳዲስና ነባር የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመተግበር የድጋፍ ስብሰባውን ያጠናክራል ነው ያለት።