በፌደራል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በመንግስት መካከል የጋራ ጉባኤ ተመሰረተ

335

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በፌደራል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በመንግስት መካከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል የትብብር ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተቋቁሟል።

በመድረኩም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

ጉባኤው በዋናነት በፖሊሲና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የፌዴራል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የመንግስት የትብብር መድረክ መሆኑ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ፣ በመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ጉባኤ መቋቋሙ ሁለቱም አካላት ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህም በሁለንተናዊ የሀገራዊ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር እንዲሁም፣ የዜጎችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግሰት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመስራት የጉባኤውን ዓላማ ለማሳካት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ፣ የጉባኤው ዓላማ በፌዴራል መንግስቱ የሚመለከታቸው አካላትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዘላቂ ሰላም፣ አካታች ልማት፣ መልካም አስተዳደር እና ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ማስቻል የጋራ ጉባኤው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መለሰ በበኩላቸው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለልተኛ የሆነ አቋማቸውን በመጠበቅ ለሀገር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋገጠዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የመንግስት የጋራ ጉባኤ በክልሎች ደረጃ ከዚህ ቀደም ተቋቁሞ በተግባር ላይ ሲሆን፤ ዛሬ የተመሰረተው በፌደራል ደረጃ መሆኑ ተጠቅሷል።

ይህም ከፌደራል እስከ ክልል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ያሉ የመንግስት አካላትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በቅንጅት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል አዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 እየተተገበረ ሲሆን በዚህም የተሻለ የሲቪክ ምህዳር ተፈጥሯል ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም