ለኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ሕንጻ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

95

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት የተገለጸው የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ሕንጻ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

ግንባታውን ለማከናወን የሚያስችል የስምምነት ፊርማ የተከናወነ ሲሆን ግንባታው በ400 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ፤ ሕንጻው ዘመናዊና ሁለገብ ሰራዊት ለመገንባት ከተጀመሩ ስራዎች አንዱ አካል የሆነ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ስራ ላይ እንዲውል አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸው ሕንጻው ሲጠናቀቅ ለሀገር ሀብት ለሰራዊቱ ደግሞ ኩራት ይሆናልም ነው ያሉት።

የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ በበኩላቸው ግንባታው ሶስት ዘመናዊ ባለ አራት ፎቅ ሕንጻን ጨምሮ የአንድ ሻለቃ ጦር መኖሪያን ያሟላ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘመናዊ የሕንጻ ኮምፕሌክሱ ከዲዛይን ጀምሮ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመረጠ መሆኑንና ለአካባቢው ነዋሪዎችም የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በተቋራጭነት የሚገነባው ሲሆን በመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ የዲዛይን ቁጥጥር መምሪያ እንደሚቆጣጠረው ተገልጿል።

በዝግጅቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ፣ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች መገኘታቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም