በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆትና ዝርፊያዎችን ለመከላከል በቅንጀት እየተሰራ ነው--የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

234

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆትና ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ገለጹ።

የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ላይ በተደጋጋሚ ዘረፋና ስርቆት የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በባቡር መስመሩ ላይ ከፍተኛ ስርቆትና ዝርፊያ እየተፈጸመ መሆኑን መገንዘብ መቻላቸውን ነው የገለጹት።

የሃዲድ መስመሩ ብሎኖችን የመፍታት፣ ብረቶችን ቆርጦ የመውሰድና ሌሎች እኩይ ድርጊቶችን በመፈጸም የትራንስፖርት አገልግሎቱን የማወክ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ከተቋሙ ጋር በጋራ በመሆን ወንጀሎቹን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያስረዱት።

በመሰረተ-ልማቱ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተራ ወንጀሎች አለመሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ ድርጊቱ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያቋርጥ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ወንጀል ፈጽመው በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ አካላት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ ወንጀሉን ለመከላከል የፍትህ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ከሰበታ መኢሶ የሴኪዩሪቲ ሴክሽን ማናጀር አቶ ግርማ ታፈሰ በበኩላቸው በሦስት ወረዳዎች ከፍተኛ ስርቆት መፈጸሙን ተናግረዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በተደረገ ኦፐሬሽን አሁን ላይ 40 የሚሆኑ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት መስመር መሰረተ ልማት ላይ በተደጋጋሚ በሚፈፀም ዘረፋ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ማኅበሩ መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም