ቀጥታ፡

ፈረንሳይ ለመልሶ ማቋቋም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 ፈረንሳይ የሰላም ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆንና በመልሶ ማቋቋም ላይ ለሚደረገው ጥረት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

ለስራ ጉብኝት ፈረንሳይ የሚገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ከፈረንሳይ የንግድ ሚኒስትር ኦሊቪየር ቤክት ጋር ተወያይተዋል።

ዶክተር እዮብ ከንግድ ሚኒስትሩ ጋር በሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ትብብርና በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በውይይቱ ወቅት ዶክተር እዮብ ለፈረንሳይ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያከናወነችው ስላለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በግጭት አካባቢዎች እየተከናወነ ስላለው የመልሶ ማቋቋም ጥረትና በሰላም ስምምነቱ አተገባበር ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጿል።

ዘላቂ የልማት አጋር የሆነችው ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ስለምትሰጠው የልማት ድጋፍና ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የፈረንሳይ የንግድ ሚኒስትር ኦሊቪየር ቤክት በበኩላቸው የፈረንሳይና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ትብብር ከምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ ያለው መሆኑን አውስተዋል።

በቅርቡ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ውጤታማ እንዲሆን፣ የመልሶ ማቋቋሙ ጥረት እንዲሳካና የኢኮኖሚ ማሻሻያው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ መገኘታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም