ቀጥታ፡

የሆስፒታሉ ግንባታ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ለጤና ችግር መዳረጋቸውን የማጂ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

ሚዛን መስከረም 25/2011 የማጂ የመጀመሪያ ደረጃ  ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት ከተያዘለት ጊዜ በአምስት ዓመታት ዘግይቶም ባለመጠናቀቁ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ። የጤና አገልግሎት ችግራቸው አለመቃለሉንም  ገለጸዋል። ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳመለከቱት ግንባታው በአንድ ዓመት  ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው ፕሮጀክት ግንባታ ያጓተተው አካል ተጠያቂ እንዲሆን ጠይቀዋል። የማጂ ከተማ ነዋሪው አቶ ግርማ ያኩዝ  የሆስፒታሉ ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ  አንጻር በመዘግየቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው  ተናግረዋል፡፡ያዘገዩት አካላት በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል ። በአቅራቢያው አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ  ሆስፒታል ባለመኖሩ ደግሞ አገልግሎቱን ለማግኘት ከ210 ኪሜ በላይ ለመጓዝ ተገደናል ብለዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አባተ አበበ በበኩላቸው የጤና ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ የኅብረተሰቡ መሠረታዊ ጥያቄና ፍላጎት እንደሆነ አመልክተው፣ግንባታው የአካባቢውን የጤና አገልግሎት ችግር እንደሚፈታ ተስፋ የተደረገበት ፕሮጀክት አለመጠናቀቁ ተገቢ እንዳልሆነ  አስታውቀዋል፡፡ የሆስፒታሉ ግንባታ ባለመጠናቀቁ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደዳረጋቸውም ተናግረዋል፡፡ ''መንግሥት የግንባታ መጓተት ሲያጋጥም ለምን ተገቢውን ክትትልና እርምጃ አይወስድም?'' በማለት የጠየቁት አቶ አባተ፣ ይህን መሰል ክፍተቶች ህዝቡ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያሳድር  አድርጎታልና  ሊታሰብባቸው ይገባል በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የማጂ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ  ኪዳኔ  በበኩላቸወው  የሆስፒታሉ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁን የሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ በመቅረቡ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ  ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። ሆስፒታሉ ለማጂ፣ለቤሮ፣ለሱርማና ለመኤኒት ሻሻ ወረዳዎች ህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ የታቀደ ቢሆንም፤በተያዘለት ጊዜ ቢጠናቀቅ ለጤና አገልግሎት መሻሻል ይረዳ ነበር ብለዋል፡፡ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ፕሮጀክቶች ግንባታ አስተባባሪ አቶ ሳሙዔል ሸሪፎ  ፕሮጀክቱ የዘገየው በሥራ ተቋራጩ ትኩረት ማነስ እንደነበር ገልጸው፣ሆኖም  በ45 ቀናት ውስጥ የኤሌክትሪክ፣የውሃና ሌሎች ግብዓቶች እንዲያሟላ ስምምነት መደረሱን  አስታውቀዋል፡፡ ቢሮው የሆስፒታሉን ግብዓቶችና የሰው ኃይል ፍላጎት በአጭር ጊዜ ውስጥ አሟልቶ  አገልግሎት እንደሚጀምርም ተናግረዋል፡፡ የሥራ ተቋራጩ የእምነቴ እንዳሻው ኮንስትራክሽን ድርጅት ተወካይ አቶ አቤኔዘር ቢረዳው ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ያልተጠናቀቀው በግንባታ ግብዓቶች እጥረት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁን አብዛኛው የሆስፒታሉ ግንባታአካል በመጠናቀቁ የጄኔሬተር ግዥ፣ውሃ የማስገባት፣ ቀለም ቅብና አንዳንድ አነስተኛ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ በማሟላት ርክክቡን እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም