በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የሕዝብ ውሳኔ ምርጫ ውጤት ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የሕዝብ ውሳኔ ምርጫ ውጤት ይፋ ተደረገ
ጂንካ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ 428 የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የሕዝብ ውሳኔ ምርጫ ውጤት ይፋ መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ኦሞ ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በቦርዱ የደቡብ ኦሞ ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሰይፉ አየለ የድምጽ አሰጣጥ እና ቆጠራው ሂደት በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ሕዝቡ በአሁኑ ሰዓት በየምርጫ ጣቢያው በመምጣት ይፋ የተደረገውን ውጤት በመመልከት ላይ ይገኛል።
በትላንትናው እለት በደቡብ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች አዲስ ለመደራጀት በቀረበው የክልል አወቃቀር ላይ ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ መሰጠቱ ይታወቃል።
አጠቃላይ እና የመጨረሻ የሕዝበ ውሳኔ ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚገለጽ ተወካዩ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮንሶ ዞን የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ካይራሌ ካራሌ ለኢዜአ እንዳሉት ትናንት ድምጽ በተሰጠባቸው ጣቢያዎች ውጤት ተለጥፎ ለህዝብ ይፋ ተደርጓል ብለዋል።
የድምጽ መስጫ ሳጥኖችና ውጤት ዛሬ ወደ ምርጫ ክልሉ እንደሚጓጓዝና አጠቃላይ የ135 ምርጫ ጣቢያዎች ውጤት ተዳምሮ በምርጫ ክልሉ እንደሚለጠፍ ገልጸዋል።