በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ተጠናቀቀ

አርባ ምንጭ ጥር 29 ቀን 2015 (ኢዜአ..) በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ዛሬ የተካሄደው የሕዝበ ውሣኔ ድምፅ አሰጣጥ መርሃ ግብር ተጠናቆ ቆጠራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ በክልሉ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ ዞኖች እና ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ላይ ዛሬ የተካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ ድምፅ መስጠት ሂደትን በተመለከተ ዛሬ ማምሻውን ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የድምጽ አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ዛሬ ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰአት ድምፅ ሲሰጥ በ31 ማዕከላት ሥር በሚገኙ 3 ሺህ 771 ምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በጋዜጣዊ ገልፀዋል።
በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጠቱ ሂደት 12 ሰአት ላይ ተጠናቆ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲዘጉ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
በክልሉ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደው ህዝብ ውሳኔ ምርጫ ጥቂት የአሰራር ክፍተቶች ከማጋጠሙ በቀር ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወኑንና መራጩ ሕዝብም ችግር ሳያጋጥመው ድምፁን ሲሰጥ መዋሉን ገልጽዋል።
በአሁኑ ወቅት በእብዛኛው ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ መጀመሩን የጠቅሱት ሰብሳቢዋ በድምፅ አሰጣጥ ሂደት ካጋጠሙ የአሰራር ግድፈቶች መካከልም ለአካለ መጠን ያልደረሱ 18 አመት ያልሞላቸው ዜጎች በመራጭነት ተመዝግበው መገኘታቸው እንዱ መሆኑን ጠቁመዋል
በአስተዳደር አካላት በበሌ ማእከል በሶርቶ ምርጫ ጣቢያ የመታወቂያ ወረቀት የማደል የተፈፀመ የህግ ጥሰቶችንም አንስተዋል ሰብሳቢዋ።
ህዝብ ውሳኔው ሰላማዊ በሚባል መልኩ የተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ሆኖም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በነበረበት የፖሊስ ሀይል እጥረት የተነሳ ሚሊሻዎች በተወሰኑ ጣቢያዎች ላይ መመደቡን ለማወቅ ተችሏል ብለዋል ።
የእነዚህና የሌሎችም ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች መረጃ የተሰበሰበው ከቦርዱ የጥሪ ማእከልና ፥ታዛቢዎችና በቦርዱ አመራር አባላት በተደረገ ክትትል መሆኑንም አብራርተዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ እንዳሉት በአጠቃላይ በዛሬው ዕለት የተካሄደው ምርጫ በአጥጋቢ ሁኔታ ተከናውኗል።