ቀጥታ፡

አምባሳደር አየለ ሊሬ የሹመት ደብዳቢያቸውን ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር አቀረቡ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር አየለ ሊሬ የሹመት ደብዳቢያቸውን ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት አቅርበዋል።

አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅትም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስላላት ሚና እና በቀጣይ ሳምንት በአዲስ አበባ ስለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ቅድመ-ዝግጅት ዙርያ ከሊቀ-መንበሩ ጋር ተወያይተዋል።

በተጨማሪም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲጠበቅ በማድረግ በኩል ለሰጠው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አምባሳደር አየለ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነቱ አተገባበርን በሚመለከት ለሊቀ-መንበሩ ገለፃ ማድረጋቸውንና ሀሳብ መለዋወጣቸውም ተገልጿል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር በበኩላቸው ለአምባሳደሩ አዲስ የስራ ሀላፊነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እሴቶች የምታበረክተውን ወሳኝ አስተዋፅዖ እንዲሁም አገሪቱ ለአህጉራዊ ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ እየተጫወተች ላለችው በጎ ሚና ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በሌላ በኩል ሊቀ-መንበሩ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጥቅሞቿ እንዲጠበቁ ለማድረግ በህብረቱ በኩል እየተከናወኑ ስላሉ የለውጥ ስራዎችም ለአምባሳደሩ ገለፃ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም