ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን በመቀበልና ደህንነታቸውን በመጠበቅ የሚያስመሰግን ስራ እየሰራ ነው-ፊሊፖ ግራንዲ

ዳባት (ኢዜአ) ጥር 29/2015 የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን በመቀበልና ደህንነታቸውን በመጠበቅ የሚያስመሰግን ስራ እየሰራ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ገለጹ።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ የሚገኘውን የ'አለምዋጭ' የስደተኞች መጠለያ ጎበኙ፡፡

ኮሚሽነሩ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በዳባት አካባቢ ለሚገኘው 'አለምዋጭ' መጠለያ ለአገልግሎት የሚውል ቦታ በመስጠትና የስደተኞችን ደህንነት በመጠበቅ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለው ተግባር በአርዓያነት ሊወሰድ የሚችል መሆኑን አስታውሰው የአካባቢው ማሕበረሰብም መመስገን አለበት ብለዋል።

ለ'አለምዋጭ' መጠለያም ኮሚሽኑ በስደተኞች መጠለያ መሟላት የሚገባቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲሟሉ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል ሲሉም አክለዋል።

በመጠለያው የመብራት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት በበቂ መጠን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ8መቶ 80 ሺህ በላይ ስደተኞች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 22 የስደተኞች መጠለያ ይኖራሉ ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው።

በተለይም ዳባት በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ በአሁኑ ወቅት ከ28 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በመጠለያ ጣቢያው የስደተኞቹ ተወካይ አቶ ሰለሞን ተስፋማርያም በበኩላቸው መጠለያው አዲሰ በመሆኑ መሠረታዊ አገልገሎቶች እንዲሟሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

በመጠለያው የጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት፣ ለወላዶች የአምቡላንስ አገልግሎት፣ ለህጻናት አልሚ ምግብ መቅረብ እንዳለበትም አንስተዋል።

ኮሚሽነሩ ከስደተኞቹ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም