ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በዘመናዊ ወታደራዊ ቴክኖሎጂና በብቁ የሰው ኃይል የማደራጀት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ዓለም በደረሰበት የዘመኑ ወታደራዊ ቴክኖሎጂና በብቁ የሰው ኃይል የማደራጀት የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ወራት የስራ አፈጻጸምን ገምግሟል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ባቀረቡት ሪፖርት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰና ጠንካራ ቁመና እንዲኖረው በስነ-ልቦና ግንባታና ወታደራዊ ትጥቁን በማሟላት በኩል ሁለንተናዊ ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሠራዊቱን የተልዕኮ አፈፃፀም የሚያጎለብቱ የአቅም ግንባታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ሠራዊቱ ዓለም የደረሰበትን ወታደራዊ ቴክኖሎጂና እውቀት በማሟላት የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝብን ደህንነት መጠበቅ የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ተደርጓል ነው ያሉት።

የሪፎርም ስራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያን የሚመጥንና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ አደረጃጀትና አሰራር እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ባለፉት ስድስት ወራት ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በመተግበር መረጃዎችን በአግባቡ በመለየት እና በመጠቀም የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስ መቻሉን ነው የገለፁት።

በአየር ኃይል፣ በምድር ኃይል፣ በባህር ኃይልና በሳይበር ዘርፍ ጠንካራ ተቋም መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

የሀገርን ክብርና ህልውና የሚያስከብር የመከላከያ ሰራዊትን የመገንባት ተቋማዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም የመከላከያ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች ሠራዊቱን በወታደራዊ ሳይንስና እውቀት ለመገንባት በጥናትና ምርምር ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ የመከላከያ ሚኒስቴር ጠንካራ ተግባራትን ማከናወኑን ገልፀዋል።

በተለይ የሀገር ሉዓላዊነትንና ደህንነትን ከማንኛውም የውጭና የውስጥ ጥቃት ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራትን ቋሚ ኮሚቴው በመልካም አፈጻጸም መገምገሙን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ዲማ አክለውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ሳይስተጓጎል በተያዘላቸው እቅድ እንዲከናወኑ ያልተቋረጠ ጥበቃ በማድረግ ረገድ ሰራዊቱ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ የሠራዊቱን የተልዕኮ አፈፃፀም ለማጎልበት በቴክኖሎጂና በብቁ የሰው ኃይል በማደራጀት በኩል የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ጠንካራ ሠራዊትና ተቋም የመገንባት ሂደትን በአግባቡ እንደሚከታተልና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴር በስድስት ወራት አፈፃፀሙ ውጤታማ የፋይናንስና የኃብት አስተዳደር ስርዓት ለማረጋገጥ የተገበራቸው አሰራሮች በውይይቱ ላይ በጠንካራ ጎን ተነስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም