ቀጥታ፡

በዓለም አቀፉ የቴክስታይል ኤክስፖ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አማራጮች እየተዋወቁ ነው- የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 በፈረንሳይ እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ ኤክስፖ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ የንግድ ትርዒት (ኤክስፖው) ዛሬ በፈረንሳይ ተጀምሯል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ የተመራ ቡድን ኤክስፖው ላይ ለመሳተፍ ፓሪስ መግባቱ ተገልጿል።

ቡድኑ በንግድ ትርዒቱ (በኤክስፖው) ላይ ከዓለም አቀፍ የዘርፉ አምራቾችና ገዢዎች ጋር በኢትዮጵያ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

በጨርቃጨርቅ ዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክቷል።

ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው የንግድ ትርዒት (ኤክስፖ) ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተመረጡ ከ900 በላይ በአልባሳት እና ጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች እና የዘርፉ አንቀሳቃሾች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ልዑክ በቆይታው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ያለውን እምቅ የኢንቨስትመት አቅም ያስተዋውቃል ተብሏል።

በዚህም ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚጋብዝ ከኮርፖሬሽኑ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም