የኢትዮጵያ 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ለዓለም ሀገራት ምርጥ ተሞክሮ የሚሆን ነው-አኒ ዳስጉታ

89

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 የኢትዮጵያ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በአራት ዓመታት መትከል መቻል ለዓለም ሀገራት ምርጥ ተሞክሮ መሆኑን የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አኒ ዳስጉታ ገለጹ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩትን ፕሬዝዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አኒ ዳስጉታ የተመራ የልኡካን ቡድንን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አኒ ዳስጉታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በአራት ዓመታት መትከል መቻል ለዓለም ሀገራት ምርጥ ተሞክሮ የሚሆን ነው።

ለዚህ ተግባርም የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት እውቅና የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰው የአየር ንብረት ተፅዕኖንና የተሰሩ የመከላከል ስራዎች የሚያመጡትን ለውጥም በተመለከተ ሳይናሳዊ መረጃ በማጠናቀር ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ መንግስት ለመከላከል ስራው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል በአስር ዓመቱ የመንግስት የልማት እቅድ ውስጥ መካተቱን ገልጸው ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት እስትራቴጂን በመንደፍ ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ብክለት ላይ ያላት ድርሻ እጅግ አናሳ ቢሆንም ባደጉት ሃገራት ከፍተኛ ብክለት እደረሰባት ያለው ጉዳት ግን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በየአስር ዓመቱ የሚከሰተው ድርቅ አሁን ላይ በየሶስት ዓመቱ መከሰት መጀመሩንና ጎርፍና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ተከትለው በሚመጡ ችግሮች ኢትዮጵያ እየተፈተነች መሆኑን አንስተዋል።

በአራት አመታት 25 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለዉጥን ከመከላከልና የደን ሽፋንን ከማሳደግ በላይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚሰራውን አገራዊ ስራ ያገዘ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።

በቅርቡ የረዥም ጊዜ ዝቅተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት ልማት እስትራቴጂን ይፋ ያደረገቺው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ቁርጠኛ አቋም ከማረጋገጥ በላይ ተጨባጭ ለውጦችን አምጥታለች ብለዋል።

በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አቡዳቢ በሚደረገው 28ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ ተሳትፎ እንዲሁም በሌሎች ትብብር መስኮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የተጀመሩ የመረጃ ማጠናቀር ፣በሰው ሃይል አቅም ግንባታ ፥ እና መሰል ትብብር መስኮች ላይ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር ከስምምነት መደረሱን የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም