የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ድምፃቸውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መስጠታቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ድምፃቸውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መስጠታቸው ገለጹ
አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ድምፃቸውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነጻነት መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በህዝበ ውሳኔው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ድምፃቸውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነፃነት በመስጠታቸው መደሰታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የድምፅ መስጫ ካርድ በወሰዱባቸው ጣቢያዎች ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ መስጠታቸውን በማከል።
በከተማዋ ዶይሳ አሸም ሁለት ምርጫ ጣቢያ ድምፅ የሰጡት አቶ ካሳሁን ከማ በሰጡት አስተያየት ዕለቱን በጉጉት ሲጠባበቁ እንደነበረ ተናግረዋል።
ማልደው ተነስተው በድምጽ መስጫ ጣቢያው ተገኝተው ድምፅ በመስጠታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።
ድምፅ ለመስጠት ካርድ የወሰዱ ነዋሪዎች በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባም መክረዋል።
ህዝበ ውሳኔው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና የልማት ጥያቄዎችን የሚፈታ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በከተማዋ የእድገት በር ቀበሌ ነዋሪው አቶ ያፓ ያና በበኩላቸው ህዝበ ውሳኔው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ገልጸዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚፈታ፣ አካባቢያቸው በተሻለ እንዲለማ፣ የሥራ እድል አማራጮች እንደያሚሰፋና የህዝብን ተጠቃሚነት እንደሚረጋገጥ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ ሆስፒታል መንደር ምርጫ ጣቢያ ድምፅ የሰጠው አካል ጉዳተኛ ወጣት ጀማል ያሲን በበኩሉ መብቱን ተጠቅሞ ለህዝበ ውሳኔው ድምፅ መስጠቱን ተናግሯል።
ህዝቡ ከማለዳው ጀምሮ ድምፅ ለመስጠት ወረፋ ይዞ በመጠባበቅ ያሳየው ተሳትፎ እንዳስደነቀው ገልጾ፤ ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በስድስት ዞኖች እና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ከማለዳው 12:00 ሰዓት የተጀመረው ምሽቱ 12:00 ሰዓት ላይ እንደሚጠናቀቅ ጠቅሶ መራጮች ወደ ተመዘገቡበት ጣቢያ በመሄድ ድምፅ እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።